መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው-ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው-ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን ጨምሮ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ጎብኝተዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።
ማዕከሉ 12 ተቋማትን እና ከ41 በላይ አገልግሎትን በአንድ ህንፃ ማግኘት የሚያስችል ነው።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እንዲሁም የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግስታት ለህዝባቸው የተቀላጠፈ እና የተሳለጠ አገልግሎት የመስጠት ግዴታም ሀላፊነትም አለባቸው።
ይህ አዲስ ሁሉን አቀፍ የሆነ በአንድ ቦታ በርካታ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው ስራ የኢትዮጵያን የህዝብ አገልግሎት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንግስት ተአማኒነት የሚለካው በሚሰጠው አገልግሎት መሆኑን ጠቁመው፤ ከዋነኛ መመዘኛዎቹ መካከልም አንዱ መሆኑን አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ በመንግስት አገልግሎት ዙሪያ ያለው ተሞክሮ የሚያኩራራ አለመሆኑን ያወሱት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ማዕከሉ ብልሹ አሰራርን በማስቀረት እንግልትን የሚያስወግድ መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ህዝብ የሚገባውን አገልግሎት ያገኝ ዘንድ የተገነባ ትልቅ ስራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለያዩ ዓለማት ስንመለከት የምንቀናበትን ስራ በሀገራችን ተመልክተነዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህንን ላከናወኑ ምስጋና አቅርበዋል።
በራስ ባለሙያዎች በአጭር ጊዜ ወደስራ ማስገባትም ትልቅ እመርታ መሆኑን አንስተዋል።
ማዕከሉ የህዝብ እንግልትን የሚያስወግድ መሆኑን ለማሳወቅም ሰፊ የተግባቦት ስራ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።