ኤክስፖው የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት የሚያሳዩ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት ነው- ሚኒስትር መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
ኤክስፖው የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት የሚያሳዩ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት ነው- ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት የሚያሳዩ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በመጪው ቅዳሜ በይፋ የሚከፈተውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ ኢንዱስትሪዎች ያጋጥማቸው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱና የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት ማድረጉን አንስተዋል።
ንቅናቄው የአገር ውስጥ ምርት አጠቃቀም ላይም ሰፊ ለውጦች መምጣቱን ገልጸዋል።
3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በመጪው ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ-ም በይፋ እንደሚጀመር ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ምርቶች ማስተዋወቅና ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን ማስፋት የኤክስፖው ዋና ዓላማ ነው ብለዋል።
የገበያ ትስስሮችን መፍጠርና የምርት ጥራትን ለማሻሻልም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
ፈጠራን ማበረታታትም አንዱ የኤክስፖው ዓላማ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ መፍጠርም ዋነኛ ግቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በኤክስፖው ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የሚያደርጉና በአይነታቸው ልዩ የሆኑ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂዎች እንደሚቀርቡም ነው የገለጹት።
ከኤክስፖው አስቀድሞ በተለያዩ ክልሎች የተደረጉ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ታምርት የ10ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የኢትዮጵያን ምርት በማስተዋወቅ በኩል ጉልህ ሚና ነበራቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ የተለያዩ የፓናል ውይይቶች፣ የምርት ልማት ውድድሮች፣የተሻለ አፈፃፀም ላላቸው ኢንዱስትሪዎች የዕውቅና ፕሮግራም እና ሌሎችም መርሃ-ግብሮች ይከናወናሉ።
በአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአምስት ቀናት የሚካሄደውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ120 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች እንደሚገኙም በመግለጫው ተብራርቷል።
በኤክስፖው 288 ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል።
ኤክስፖውን ሁሉም ዜጋ እንዲጎበኘውና የኢትዮጵያን ምርት እንዲገዛ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።