በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉና ውጤታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉና ውጤታማ ናቸው

በደብረ ብርሃን፤ ሚያዚያ 22/2017 (ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሃን ከተማ ሰላምን በማጽናት የተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አስታወቀ።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባዔ አቶ መንግስቱ ቤተ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች አበረታች ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ የክላስተር አደረጃጀት ፈጥሮ የሚካሄዱ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን መምራት፣ መደገፍና መቆጣጠር በመቻሉ አበረታች ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል ብለዋል።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማዋ እየተካሄዱ ያሉ የአስፋልት፣ የኮብል ስቶንና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የህብረተሰቡን ጥያቄ በመለየትና አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ የተሰራው ስራ መልካም ውጤት የታየበት ነው ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደገለጹት አስተዳደሩ ማህበረሰቡን በማስተባበር ያከናወነው ሰላምን የማስፈንና ልማትን የማረጋገጥ ስራ ስኬታማ ነው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኮሪደር ልማት፣ የመብራትና የውሃ መስመር ማስፋፋት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድና ሌሎች የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
የከተማው ማህበረሰብም የልማት ስራዎቹን ለማከናወን የሚያስችል ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል።
በተለይም በ83 ማህበራት ለተደራጁ የከተማዋ ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱ የከተማዋን ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ የፈታ ስኬታማ ስራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን በኢንቨስትመንት፣ በከተማ ግብርና፣ በንግድ፣ የኑሮ ውድነትን በመቀነስና በሌሎች ተግባራት ውጤታማ ስራ እንደተሰራ አብራርተዋል።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ14 ሺህ 22 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመው ለስራ እድል ተጠቃሚዎችም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ፣ ብድርና ሌሎች ድጋፎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።