ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት እንድትቀላቀል አሜሪካ ድጋፍ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት እንድትቀላቀል አሜሪካ ድጋፍ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ አሜሪካ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት እንድትቀላቀል ድጋፍ እንደምታደርግ የአሜሪካ የንግድ ፅህፈት ቤት ተወካይ ኒል ቤክ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በተሳካ ሁኔታ ከዓለም አቀፉ የግብይት ሥርዓት ጋር መዋሃድ የአሜሪካ ፍላጎት ነውም ብለዋል።
የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በአሜሪካ የንግድ ፅህፈት ቤት የዓለም ንግድ ድርጅት እና የባለ ብዙ ወገን ጉዳዮች ረዳት ተወካይ ኔል ቤክ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት ለመቀላቀል እያደረገች ያለውን ከፍተኛ ጥረት አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።
እ.ኤ.አ. በማርች 2026 ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች ለማሟላት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ኔል ቤክ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያከናወነች ያለውን ከፍተኛ ጥረት አድንቀው፤ የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት እንድትቀላቀል አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተሳካ ሁኔታ ከዓለም አቀፉ የግብይት ሥርዓት ጋር መዋሃድ የአሜሪካ ፍላጎት ነው ብለዋል።
ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው ጉዞ ላይ ትብብራቸውን ለመቀጠልና አጋርነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ አመልክቷል።