የአዳማ ከተማን የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ለማሳለጥ የአንድ ማዕከልና ዲጂታል አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ ከተማን የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ለማሳለጥ የአንድ ማዕከልና ዲጂታል አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ ነው

አዳማ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦የአዳማ ከተማን የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ለማሳለጥ የአንድ ማዕከልና ዲጂታል አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ገለፁ።
ከተማ አስተዳደሩ ከባለሃብቶች ጋር በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ምክክር አድርጓል።
ከንቲባው በወቅቱ እንደገለፁት፥ መንግሥት የአሰራርና የህግ ማዕቀፎችን በአዲስ መልክ በማዘጋጀት የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ሁሉንም ባማከለ መልኩ እንዲከናወን እየተደረገ ነው።
ባለፉት ዓመታት በአስተዳደሩ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት መግባታቸውን ገልጸው፥ ውጤታማነታቸውም የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት እውን በመደረጉ፣በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘና ሌሎች ዘመናዊ አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸው ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሽ መሆኑን የገለፁት አቶ ሀይሉ፤ የመሰረተ ልማት አቅርቦትም የተሻለ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ነው የገለጹት።
ከመሰረተ ልማቶቹ መካከል አዳማ ወንጂ የአስፋልት መንገድ፣ የአዳማ አዋሽ መልካሣ የአስፋልት መንገድ ደረጃ የማሻሻል ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የመብራት፣ የውሃ፣ የመሬትና የብድር አቅርቦት ዙሪያ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር መደረጉንም ነው የተናገሩት።
አስተዳደሩ በሌብነትና ብልሹ አሰራር ውስጥ የተሳተፉ አመራሮች፣ የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አያይዘውም፥ መሬት አጥረው በሚያስቀምጡ ባለሃብቶች፣የተጓተቱ ፕሮጀክቶችና የገነቡትን የኢንዱስትሪ ሼዶች ለመጋዘን አገልግሎት ያዋሉ ባለሃብቶች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
የአዳማ ከተማ ባለሃብቶች ፎረም ሰብሳቢና የአዳማ ቆሮቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ አብዱልሃኪም ሙሐመድ በበኩላቸው፥ ፎረሙ የባለሀብቶችን ጥያቄዎች ለመመለስ ከአስተዳድሩ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።