በክልሉ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የልማት ስራዎችን ለማፋጠን የወጣቶች ሚና የጎላ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ሚያዚያ 22/2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑ ተገለፀ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ ከቴክኒክና ሙያ ተማሪዎች ጋር በዘላቂ ሰላም ግንባታ ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት የኢኮኖሚ ክላስተር አማካሪ አቶ አስናቀ ይርጉ እንዳሉት፤ ወጣቱ የአገር ተረካቢነት ሚናውን ለመወጣት ለሰላም ዘብ መቆም አለበት።


 

በተለይም የክልሉን ህዝብ አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ ሃይሎች ችግርን በመፍጠር ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ማድረጋቸው፣ ሰብዓዊ፣ማህበራዊ እና ቁሳዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ውድመት ማድረሳቸውን አስገንዝበዋል።

ስለሆነም እነዚህን ኃይሎች በመታገል አሁን የተገኘውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ሽባባው በበኩላቸው፥ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ጋር በተደረገ ተደጋጋሚ ውይይት በከተማዋ ሰላም እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

ይህንን ሰላም በማዝለቅም በየአካባቢው የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ለውጤታማነቱም ወጣቶች ጉልህ ሚናቸውን በማበርከት ለከተማቸው ሰላም ዘብ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በከተማው በተደረገው ውይይት የተሳተፉ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎችም የመማር ማስተማር ስራው ስኬታማ እንዲሆን ለሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

''የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ" በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የውይይት መድረክም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተማሪዎችና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም