በድሬደዋና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ህፃናት 160 ዊልቸር ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ህፃናት 160 ዊልቸር ድጋፍ ተደረገ

ድሬደዋ፣ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ) በድሬደዋና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ህፃናት 160 ዊልቸር ድጋፍ ተደረገ።
የድሬደዋ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሁክሚያ መሐመድ በወቅቱ እንዳሉት፤ ቢሮው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በህፃናት ላይ የሚደርሱ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል።
ህፃናቱ ያሉባቸውን የምግብ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል ቀጣዩ ህይወታቸው እንዲለመልም እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ዛሬም ፋውንዴሽኑ ለአካል ጉዳተኞች ያደረገው ድጋፍም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ መሰል የበጎ አድራጎት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ድጋፉን ያደረገው የፋጡማና ኬኛ ፋውንዴሽን የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ተሬዛ አሜ በበኩላቸው ህፃናት ያሉባቸው ችግሮች የማቃለል ስራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ካለው ላይ በመለገስ የተሻለ ህይወት እንዲመሩ መደገፍ ይኖርበታል ብለዋል።
ፋውንዴሽኑ በ56 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የተገዙ ዊልቸሮች ድሬደዋና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ህፃናት ማከፋፈል መጀመሩን ገልጸዋል።
በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ድጋፉን ለህፃናቱ የሰጡት የድሬደዋ አስተዳደር ምክርቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ሻኪር አህመድ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።