ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ የኢንዱስትሪዎች ምርታማነት እንዲያድግና ኢንቨስትመንት እንዲጨምር አስችሏል- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ የኢንዱስትሪዎች ምርታማነት እንዲያድግና ኢንቨስትመንት እንዲጨምር አስችሏል- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአማራ ክልል የኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ከማሳደጉም በተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት ምርታማነታቸውን ማሳደግ የሚያስችለውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ሚያዝያ 2014 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ሀገራዊ ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ውስብስብ ችግሮች በቅንጅት በመፍታት ተወዳዳሪና ምርታማ ማድረግ አስችሏል።
በዚህም ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ወጪን በመቀነስ የምርት ጥራትና አቅርቦትን ያሳለጠ ውጤታማ ንቅናቄ ሆኗል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ንቅናቄው መጀመሩን ተከትሎ በክልሉ በርካታ ዞኖች ከተማ አስተዳደሮች የንቅናቄ መድረክ መካሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ከዚህ ቀደም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት እንቅፋት የሆኑ ችግሮች መቅረፍ የተቻለ ሲሆን መንግስትና ባለሀብቱ በቅርበት በጋራ እንዲሰሩ ምቹ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በክልሉ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ከማድረጉም በተጨማሪ ኢንቨስትመንቱ እንዲስፋፋ ማድረጉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ንቅናቄው የስራ እድል እንዲሰፋ እንዲሁም ሌሎች ለክልሉ እድገት አስተዋጾ የሚያደርጉ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አድርጓል ብለዋል።
በበጀት አመቱ ብቻ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተከትሎ የተገኙትን ውጤቶች ርዕሰ መስተዳድሩ ለአብነት አንስተዋል፡፡
የገቢ ምርትን በመተካት በኩልም 324 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት ማምረት መቻሉን አንስተዋል፡፡
እንዲሁም 50 ሺህ 772 የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ52 ሺህ 772 ዜጎች ስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
የመሰረተ ልማት ጥያቄ የሆኑት ለአምራቹ ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ የመብራት፣የውሃና ሌሎች ጥያቄዎች በፍጥነት መልስ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ምንም እንኳን በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የጸጥታ ችግር ቢኖርም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እየጨመረ ባለሀብቱ በካፒታል መጠኑ እንዲያድግ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልሉ በትክክል ያለውን ጸጋ እንዲያስተዋውቅ በማገዝ ውጤታማ እያደረገው ይገኛል ብለዋል።