የመምህራንን አቅም በመገንባት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው-ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል እና የመምህራንን አቅም በመገንባት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።

"በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።

የትምህርት ሚኒስቴር፣የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካን ብሬይን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አህጉራዊ ጉባኤ በአፍሪካውያን በትምህርት፣ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በስራ ፈጠራ እና ስታርት አፕ ሪፎርም፣ አቅም ግንባታ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር መፍጠር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ተጠናቋል።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ጉባኤው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመሰረተ ልማትና መምህራን አቅም ግንባታ ላይ ገንቢ ውይይት የተደረገበት ነው።

በጉባኤው ላይ የተነሱ ሀሳቦች የመምህራንን አቅም ለመገንባትና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው ብለዋል።

በአፍሪካ ዘላቂና ጥራት ያለው የልጆች ትምህርት ስርዓት ለመገንባት አቅም ግንባታ፣ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የአጭርና ረጅም ዘመን እቅድ ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል።

አፍሪካ በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ከሁኔታዎች ጋር መራመድ ካልቻለች የከፋ ነገር ይገጥማታል ብለዋል።

በመሆኑም ዘመኑን የዋጀ ዝግጅት በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸች አፍሪካን እውን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ትምህርት የሁሉም ነገር ቁልፍ መሆኑን በመግለጽ፣ በመደበኛ ትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትምህርት መሰረተ ልማት እና መምህራን አቅም ግንባታ ተጨባጭ ስራ ጀምራለች ብለዋል።

አፍሪካውያን ከአጋር ተቋማት ጋር ያላቸው ትብብር መጠናከር ያለበት ቢሆንም፣ከአህጉሪቱ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር መቃኘት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም