የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በርካታ ትሩፋቶችን አስገኝቷል - ከንቲባ ከድር ጁሀር

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በርካታ ትሩፋቶችን ማስገኘቱን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ገለጹ።

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ሀገራዊ የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቷል።

እቅዱንም ለማሳካት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዋነኛው ነው።

ባለፉት አመታትም ይህንን የልማት ጉዞ በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎች እና ፖሊሲዎች ተነድፈው ወደ ትግበራ ገብተዋል።

ይህም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ በከፍተኛ ሁኔታ  እያደገ ይገኛል።

እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በ2014 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጀምሯል።

ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርታማነት ንቅናቄዎች የተካሄዱ ሲሆን ስለኢንዱስትሪ ምርታማነት ሰፊ ግንዛቤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲፈጠር አድርጓል።

ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማምረት እንዲሁም የግብርና እና ማዕድን ምርቶች ላይ ዕሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ንቅናቄው በድሬደዋ ከተማ በርካታ ትሩፋቶችን ማስገኘቱን ገልጸዋል።

በተለይም ተኪ ምርቶችን በማምረት ላይ በርካታ ኢንዱስትሪዎች መሰማራታቸውን ገልጸው፤ ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችም ወደ ምርት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በሰራ ፈጠራ ረገድም በርካታ ወጣቶች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪዎች የስራ እድል እየተፈጠረላቸው መሆኑን  ተናግረዋል።

ከንቲባ ከድር ጁሀር አስተዳደሩ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የማሳደግ ስራዎች መከናወናቸውን እና እነዚህም በራስ አቅም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በተኪ ምርትና ኤክስፖርት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ከ5 ወደ 12 ከፍ ማለታቸውንም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም