የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በመጪው ቅዳሜ በይፋ ይከፈታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በመጪው ቅዳሜ በይፋ ይከፈታል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦የ2017 ዓ-ም ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ በይፋ እንደሚከፈት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ኤክስፖውን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች ያጋጥማቸው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱና የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት ማድረጉን አንስተዋል።
ንቅናቄው የአገር ውስጥ ምርት አጠቃቀም ላይ ሰፊ ለውጦች መምጣታቸውን ገልጸዋል።
3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በመጪው ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ-ም በይፋ እንደሚጀመር ገልጸው፥ የኢትዮጵያን ምርቶች ማስተዋወቅና ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን ማስፋት የኤክስፖው ዋና ዓላማ ነው ብለዋል።
የገበያ ትስስሮችን መፍጠርና የምርት ጥራትን ለማሻሻልም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
ፈጠራን ማበረታታትም አንዱ የኤክስፖው ዓላማ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ መፍጠርም ዋነኛ ግቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ ክልሎች የተደረጉ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የኢትዮጵያን ምርት በማስተዋወቅ በኩል ጉልህ ሚና ነበራቸው ብለዋል።
በኤክስፖው 288 ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል።
በአዲስ አለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአምስት ቀናት የሚካሄደውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ120 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች እንደሚኖሩም በመግለጫው ተብራርቷል።
በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ የተለያዩ የፓናል ውይይቶች፣የምርት ልማት ውድድሮች፣የተሻለ አፈፃፀም ላላቸው ኢንዱስትሪዎች የዕውቅና ፕሮግራም እና ሌሎችም መርሃ-ግብሮች ይከናወናሉ።