በክልሉ በዘንድሮው የመኸር ወቅት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን ታቅዷል

አሶሳ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ):- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ባበክር ሃሊፋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥በዘንድሮው የመኸር ወቅት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በዘር ይሸፈናል።

በአሁኑ ወቅት የማሳ ዝግጅት በሁሉም አካባቢዎች በመካሄድ ላይ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።

አርሶ አደሩም የኩታ ገጠም እርሻን ጥቅም በመረዳቱ ዘንድሮ በስፋት በዚሁ የግብርና ስነ-ዘዴ ለማልማት የሚያስችል የማሳ ዝግጅት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ስራውን በማዘመን ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይም በስፋት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በግብርናው ዘርፍ ጥሩ አፈጻጸም በታየባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች እና ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን አቶ ባበክር ተናግረዋል።

የግብርና ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በክልሉ የሚገኙ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ፣ በግብርና ፍኖተ ካርታ እና ወቅታዊ የግብርና ስራዎች ላይ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውንም አክለዋል።

በዘንድሮው ዓመት ለክልሉ ከተመደበው 231 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 100 ሺህ የሚጠጋ ኩንታል ወደ ክልሉ መግባቱን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥም 15 ሺህ ኩንታሉ መሰራጨቱን ጠቁመው፥ አርሶ አደሩ ግብዓቱን በወቅቱ ሊጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሌላ በኩልም ከአራት ሺህ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ወደ ክልሉ መግባቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ምንም አይነት የግብዓት እጥረት እንደማይገጥመው ያረጋገጡት ኃላፊው፥ ለመኸር እርሻ የጀመረውን ዝግጅት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም