ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራዎች የምናደርገውን ድጋፍ እናጠናክራለን-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራዎች የምናደርገውን ድጋፍ እናጠናክራለን-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎች

ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዚያ 22/2017 (ኢዜአ):-ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ እስከ 600 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በክልሉ የወላይታ፣ የጌዴኦ እና የጋሞ ዞኖች ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ሥራዎች የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ በቀለ ግምጃ እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያንን ከዳር እስከ ዳር ያስተሳሰረ የአንድነት ምልክት ነው።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ የግድቡን ግንባታ ቀሪ ሥራዎች ለማጠናቀቅም በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ነዋሪ ወጣት ተመስገን መኮንን በበኩሉ በኢትዮጵያውያን ትብብር ግንባታው ሲከናወን የቆየው የሕዳሴው ግድብ ወደ መጠናቀቅ በመድረሱ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል።
የግድቡ መጠናቀቅ በቱሪዝምና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ ግድቡ እኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመጪው ትውልድ "የአንድነት ውጤትን የምናሳይበት ቅርስ ነው" ያሉት ደግሞ በጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አዳነች ጩርቦ ናቸው።
የሕዳሴው ግድብ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ የሃይል አቅርቦት ችግርን ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ "የበኩሌን ድጋፍ አጠናክራለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዘርፉ አጥናፉ እንዳሉት በከልሉ በበጀት ዓመቱ ለግድቡ ግንባታ ቀሪ ሥራዎች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ እየተሠራ ነው።
በዚህም ባለፉት አራት ወራት በተደረገው ንቅናቄ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለመሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የክልሉ ህዝብ ለሕዳሴው ግድብ በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ አሻራውን ማኖሩን አስታውሰው፣ ይህም የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማዳበር ማስቻሉን ተናግረዋል።
የግድቡ ቀሪ ሥራ እንዲጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት የክልሉን ህዝብ በማስተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
በክልሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከ670 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ከማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።