የቴምር ምርትን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል-ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የቴምር ምርትን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል-ግብርና ሚኒስቴር

አይሳኢታ፤ሚያዝያ 22/2017 (ኢዜአ)፦የቴምር ምርትን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአፋር ክልል አይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች ላይ እየተከናወነ ያለው የቴምር ልማት የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች ከሊፋ ዓለም ዓቀፍ የቴምር ልማትና ምርምር ተቋም ተወካዮች በተገኙበት የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።
ሚኒስቴሩ ከሊፋ ዓለም ዓቀፍ የቴምር ልማትና ምርምር ከተባለው የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ተቋም ጋር በመሆን አይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች ላይ ምርቱን ለማስፋት እና የምርምር ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኑም ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፥በአፋር ክልል የቴምር ምርቶችን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ጅምር ሥራዎቹን የአገሪቷ ሥነ ምህዳር በሚስማማባቸው ክልሎችና ዞኖች ለማስፈት የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ እንደ አገር በቴምር ላይ በተደረገ ምርምር ሁለት ዝርያዎች መውጣታቸውን ተናግረዋል።
አስራ አራት የሚሆኑ ዝርያዎች ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ጋር በመሆን ለማውጣት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የቴምር ፍላጎት እንደ አገር በተለይም በፆም ወራት እየጨመረ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይ በስፋት ከተሰራ ከውጭ የሚገባውን ቴምር በአገር ውስጥ መተካት የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።
በዋናነት አፋር ክልል አይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች ለልማቱ ተመራጭ መሆናቸውን ገልጸው፥የሶማሌና ጋምቤላ ክልሎችም በዚህ ረገድ ምቹ ሥነምህዳር እንዳላቸው ገልፀዋል።
የአፋር ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ምክትል ሐላፊ አቶ ኡስማን መሐመድ እንዳሉት፥ በአይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች አገር በቀል የሆነና 300 ዓመታትን ያስቆጠረ የቴምር ዝርያ መኖሩን አመልክተዋል።
ይህም በምርምር በመታገዝ ምርታማነቱን በማሳደግ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አኳያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዕለቱ የተገኙት የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሐመድ ኡስማን (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በምግብ ራስን ለመቻል ከሚደረጉት ጥረቶቾ አንዱ የቴምር ምርት ላይ የሚሰራውን ሥራ ማጠናከር ነው።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ስራ ተገብቶ 2 ሺህ 500 ሄክታር ላይ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው፥ በቀጣይ 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊዮን የቴምር ዛፎችን መትከል ዓላማ ያደረገ ስራ ታቅዶ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑሩ፣ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች እንዲሁም የሠመራ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ተገተኝተዋል።