የኮሪደር ልማት ስራው የመዲናይቱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በሚያሳድግ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦የኮሪደር ልማት ስራው ለዜጎች የዘመነች ከተማን ብሎም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን በሚያሳድግ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

በዚህም የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለጥያቄዎቹ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

ከንቲባዋ የኮሪደር ልማት ስራን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ የለውጡ መንግስት መዲናዋን እንደስሟ ውብ እና ጽዱ የማድረግ ተግባር በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በተገባው ቃል መሰረት አዲስ አበባን ለነዋሪዎቹ ምቹ እንድትሆን ብሎም አለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷን ከፍ ለማድረግ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም አንድ ከተማ ተወዳዳሪ ለመሆን ማሟላት ያለበት መስፈርቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህም መስፈርቶች መካከል የመሰረተ ልማት ጥያቄ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም የፍሳሽ አወጋገድ ስርአት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የትራንስፖርት እና የአረንጓዴ ሽፋን ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከዚህ አንጻር አዲስ አበባ ያለባትን ክፍተት ለመፍታት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

ህዝቡ ውብ፣ ጽዱ እና ለጤና ተስማሚ በሆነ አካባቢ እንዲኖር አቅም እና ልጆችን ለማሳደግም ምቹ መደላድልን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋን የአረንጓዴ ልማት ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር የኮሪደር ልማት ስራው የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፤ ለዜጎችም በርካታ የስራ እድል የፈጠረ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም