ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከስራ ውጭ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ አስችሏል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከስራ ውጭ የነበሩና የተቀዛቀዙ ኢንዱስትሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንዲገቡ ማስቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ በ7 ከተሞች ከ2ሺህ ሄክታር በላይ ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ቦታዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ሚያዚያ 2014 ዓ.ም ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ንቅናቄው በኢትየጵያ የተለያዩ ምርቶች እንዲመረቱ ከማስቻሉ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በማስቀረት በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር በክልሉ ከ569 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚገኙበት ደረጃ ተለይቷል።

በዚህም በተሟላ መልኩ የሚሰሩ፣ በአነስተኛ ደረጃ የሚሰሩና ማምረት ያልጀመሩ ኢንዱስትሪዎች መለየታቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን መሰረት በማድረግ በተከናወኑ ስራዎች ወደ ስራ ያልገቡና የተቀዛቀዙ አብዛኛው ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ንቅናቄው የውጭ ምርቶች በሀገር ውስጥ የመተካት ስራዎችና ሰፊ የስራ እድል ፈጠራ እንዲጨምር አድርጓል።

የመሰረተ ልማት፣ የአገልግሎት ሰጪ እና የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አስተዋጽኦ ማድርጉንም ገልጸዋል።

ንቅናቄው የማምረት አቅማቸውን በመጨመር ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገሩ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ ተጨማሪ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በአግባቡ የመለየት ስራዎች በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በክልሉ በ7 ከተሞች ከ2ሺህ ሄክታር በላይ ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ መሰረተ ልማት የማሟላትና ሌሎች የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም