ከመስኖ ልማት የምናገኘው ምርት ከፍጆታችን ባለፈ ለገበያ እያቀረብን ገቢያችንን እያሳደግን ነው - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ከመስኖ ልማት የምናገኘው ምርት ከፍጆታችን ባለፈ ለገበያ እያቀረብን ገቢያችንን እያሳደግን ነው - አርሶ አደሮች

ደብረ ማርቆስ፤ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ በመስኖ ልማት ላይ በመሳተፍ የሚያገኙት ምርት ከፍጆታቸው አልፎ ለገበያ በማቅረብ ኑሯቸውን እያሻሻሉ መሆኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዘንድሮ የበጋ ወቅት ከ35ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል በመስኖ መልማቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አመልክቷል።
አርሶ አደር በቃሉ ምስጋናው በዞኑ አነደድ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ፤ መስኖን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ቀደም ሲልም ከመስኖ ልማት የሚያገኙት ምርት ከቤተሰባቸው ፍጆታ አልፎ ምርቱ ለገበያ ሲያቀርቡ እንደቆዩ አስረድተዋል።
በዘንድሮ የበጋ ወቅትም ከግማሽ ሄክታር በላይ ማሳቸው ላይ በመጀመሪያው ዙር መስኖ ያለሙትን የድንች ምርት በመሸጥ ከ50ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት ካለሙት የድንች ሰብል ከ30ሺህ ብር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የማቻከል ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ይበልጣል አዘነ በበኩላቸው፤ በመስኖ ልማት ላይ በመሳተፍ በምግብ ራሴን ከመቻል ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ በቅቻለሁ ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በመስኖ ልማት በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ በማምረት ኑሯቸውን ከማሻሻል በተጨማሪ በደብረ ማርቆስ ከተማ ቤት መግዛት እንደቻሉም አውስተዋል።
በዚህ ዓመትም የጓሮ አትክልቶችን፣ በቆሎና የበጋ ስንዴ ማልማታቸውን ጠቁመው፤ ምርቱም ደርሶ እየሰበሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከፍጆታቸው የተረፈውን ምርት በመሸጥ ከ90ሺህ ብር በላይ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ሃብታሙ አህመድ እንደገለጹት፤ በመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በዘንድሮ የበጋ ወቅት በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት ከ38ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያየ ሰብል ለማልማት ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተደረገ ጥረት እስካሁን ከ35ሺህ ሄክታር በላይ ማልማት መቻሉን አመልክተዋል።
ከ100ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በተካሄደው የመስኖ ልማት እስካሁን ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ፣ የገብስ፣ የጓያ፣ የበቆሎና የተለያየ የአትክልት ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የመስኖ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግ በግብአትነት ከ52ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ማዋሉን አስታውሰዋል።
የግብርና መምሪያው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባለፈው ዓመት በመስኖ ከለማው ማሳ ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል።