የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎታችንን እንድናዳብር አስችሎናል - ሰልጣኞች

ሐረር፤ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን ማዳበር እንዳስቻላቸው በሐረሪ ክልል የዘርፉ ሰልጣኞች ገለጹ።

የኢትዮ ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና በተቀናጀ መልኩ መከናወኑ ውጤት ማስገኘቱን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።


 

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዲጂታል ዘመኑ ራሳቸውን ብቁ በማድረግ ተወዳዳሪ ለመሆን አግዟቸዋል።


 

ስልጠናውን ከተከታተሉ መካከል ሳምራዊት ዓለሙ እንደገለጸችው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎቷን አሳድጎላታል።

ስልጠናው በመረጃ ራሷን ለማበልጸግ እንዳገዛትም ተናግራለች።


 

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናው የቴክኖሎጂ ክህሎትን ለማዳበር እንደረዳት የገለጸችው ደግሞ ሌላዋ ሰልጣኝ ተማሪ ሱመያ አስክንድር ናት።

ስልጠናው በቴክኖሎጂ የበቃ ወጣትን ለመፍጠር አጋዥ በመሆኑ ወጣቶች መንግስት ያመቻቸውን እድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸውም መክራለች።


 

የሐረሪ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም በበኩላችው በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ በሶስት ዓመት 27ሺህ ወጣቶች ለማሰልጠን ታቅዶ እየተሰራ ነው።

በዘንድሮ በጀት አመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በተከናወነ ስራም ከ7ሺህ 300 በላይ ወጣቶች ስልጠናውን መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል።

ከሰለጠኑት መካከል ከግማሽ በላዮቹ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሰርተፍኬት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ጀማል ገለጻ በክልሉ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች ስለ ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተከናውኗል።

በተጨማሪም ከተለያዩ ተቋማት፣ የግልና የመንግስት ኮሌጆች፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ጋር የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር ለውጤታማነቱ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን አስታውቀዋል።


 

በክልሉ በየደረጃው ያለው አመራር ለኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ትኩረት መስጠቱ ለስኬታማነቱ ተጨማሪ አቅም መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኤጀንሲው የኢትዮ ኮደርስ ቴክኖሎጂ አሰልጣኝ አቶ እድሪስ ሰፋ ናቸው።

ሰልጣኝ ወጣቶችም በስልጠናው የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን በማዳበር ራሳቸውን ከዲጂታል ዓለም ጋር ለማስኬድ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም