ተደራጅተን የአካባቢያችንን ሰላም ማፅናት መቻላችን ልማት ሳይስተጓጎል ማስቀጠላችን ተጠቃሚ አድርጎናል - የጎንደር ነዋሪዎች

ጎንደር፤ ሚያዚያ 22/2017(ኢዜአ)፡- ተደራጅተን የአካባቢያችንን ሰላም ማፅናት መቻላችን የትምህርትና የግብርና ተግባርን ጨምሮ ሌላውም ልማት ሳይስተጓጎል በማስቀጠል ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ የጎንደር ከተማ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ለጸጥታ መዋቅሩ ተጨማሪ አቅም መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ገልጿል። 

በከተማው የሳይና ሳቢያ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አቶ አለሙ ቢያድግልኝ፤  ሰላምን ማፅናትና  ልማትን ማስቀጠል የመንግስት ብቻ ሃላፊነት አለመሆኑን በመገንዘብ ለሰላም አጥብቀን በመስራታችን የአካባቢያችንን የተሟላ ሰላም ማረጋገጥ ችለናል ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም ተደራጅተን የአካባቢችንን ሰላም በማፅናታችን በቀበሌያችን የሚገኘው ትምህርት ቤት ሥራ ሳይስተጓጎል  ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩ ማድረግ ችለናል ነው ያሉት፡፡

ፅንፈኛው ቡድን  በመንግስትና የሕዝብ  ተቋማት ንብረቶች ላይ ዘረፋና ውድመት እንዳይፈጽም ባደረግነው ጥበቃ  የተሟላ የመንግስት አገልግሎት እያገኘን ነው ብለዋል፡፡


 

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጓዴ አደራጀው፤ ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በመረዳት የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የግብርና ስራቸውን በተሟላ መንገድ እያካሄዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በመረከብ የመኸር እርሻ ዝግጅት መጀመራቸውን ጠቁመው፤ በበጋው ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማትና የመስኖ ልማት ስራ ማከናወን እንደቻሉም ጠቅሰዋል፡፡


 

ተደራጅተው ሰላምን ጠብቀው ማፅናት በመቻላቸው በአካባቢያቸው የትምህርት፣ የጤና አገልግሎትና  ሌላም የልማት ተግባር ሳይስተጓጎል በመቀጠል ተጠቃሚ እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ፈንታ ገድሉ ናቸው፡፡

ፅንፈኛው ቡድን ትምህርት ቤት ተዘግቶ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ሙከራ ቢያደርግም ተደራጅተን ሰላማችን በመጠበቃችን ልጆቻችን ዛሬ ላይ ትምህርታቸውን ተከታትለው ለዓመቱ ፈተና እየተዘጋጁ ናቸው ብለዋል፡፡ 


 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር  ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ አለልኝ አለም በበኩላቸው፤ የከተማውና ዙሪያ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች በብሎክ በመደራጀት ሰላማቸውን በማረጋገጥ የተጀመሩ ልማቶች እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ እንደቻሉ አረጋግጠዋል።

ህዝቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ፅንፈኛው ቡድን በእገታ ወንጀል በሚያሰማራቸው የጥፋት ተላላኪዎች የከተማውን ሰላም ለማደፍረስ ሙከራ ያደረጉትን በመያዝ ለህግ በማቅረብ ጠንካራ የሰላም የማስከበር ስራዎችን ሰርተዋል ነው ያሉት።

ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ለጸጥታ መዋቅሩ ተጨማሪ አቅም በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም