ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን - የመቱ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን - የመቱ ወረዳ ነዋሪዎች
መቱ፤ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ የሚያደርጉትን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢሉባቦር ዞን የመቱ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በዞኑ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ድጋፍ በተለያየ መልኩ መቀጠሉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
በዞኑ ኢዜአ ያነጋገራናቸው የመቱ ወረዳ ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዢና በገንዘብ የሚያደርጉት ድጋፍ የግንባታው መጠናቀቅ የመጨረሻ ብስራት እስከሚሰማበት ዕለት ድረስ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ታምራት ሀብታሙ በወረዳው የመንግሥት ሰራተኛ ሲሆኑ እስካሁን በተለያዩ ጊዜያት ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አሁንም የግንባታው መጠናቀቅ እስከሚሰማበት ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ወጣት ኢሳያስ ባትሪ በበኩሉ እንደማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ወጣት በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በተለያዩ መልኩ እየተሳተፈ እንደምገኝ ገልጿል።
ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ቦንድ በመግዛት የበኩሉን አሻራ ሲያኖር መቆየቱን በመግለጽ በቀሪዎቹ ጊዜያትም የአቅሙን ሁሉ ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግሯል።
አቶ ዓለማየሁ ተካ እና ወጣት ይሁን ተፈሪ በተመሳሳይ የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት እና የአንድነታችን መገለጫ በሆነው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፉት ዓመታት ሲያደርጉ የነበሩትን ድጋፍ አሁንም እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በአንድነታችን እዚህ ያደረስነው ይህን ሀገራዊ ፕሮጀክት ለሌሎች ትላልቅ ሀገራዊ የልማት ስራዎች በጋራ ተረባርበን እድገትና ተጠቃሚነታችንን ማረጋገጥ እንዳለብን የተማርንበት ነው ሲሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዞኑ ነዋሪዎች በገንዘብ ድጋፍ እና በቦንድ ግዥ ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኢሉባቦር ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶለሳ አሰፋ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በተደረገው ተሳትፎም ከዞኑ ነዋሪዎች 123 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡን ጠቁመው፤ በተያዘው ዓመትም 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቦንድ ግዢ እና በገንዘብ ድጋፍ በሚደረገው ተሳትፎ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የበኩሉን በመወጣት ላይ እንደሚገኙም አክለዋል።