ኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል የኢኖቬሽንና የፈጠራ ሥነ ምህዳር እየገነባች ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል የኢኖቬሽንና የፈጠራ ሥነ ምህዳር እየገነባች መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

"ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025" የአፍሪካ የትምህርት፣ አይሲቲ እና ክህሎት የሚኒስትሮች ስብሰባ " በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የትምህርት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴሮች ከአፍሪካን ብሬይን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አህጉራዊ ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል።

የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ አፍሪካን በትምህርት፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በክህሎት ልማትና ሥራ ፈጠራ ለማስተሳሰር ያለመ ነው።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል "ለክህሎት ልማትና አዲስ መወዳደሪያ ለአፍሪካ አፍላቂዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ንግግር አድርገዋል።

ሚኒስትሯ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በኢንዱስትሪዎች፣ ሲቪል ማህበራት፣ በትምህርት ተቋማት መካከል ትብብር በመፍጠር ክህሎትን ለማሳደግ እና የፖሊሲ ግብዓት ለማሰባሰብ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ወጣቶች በስራ ፈጠራ፣ ኢኖቬሽን እና ክህሎት ልማት የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የሥራ ፈጠራ ለወጣቶች ከእጅ ወደ አፍ ያለፈ መሆን አለበት ያሉት ሚኒስትሯ፣ አዳዲስ የፈጠራ ክህሎትን ማዳበር ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአፍሪካ አካታችና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ አይሲቲ ዘርፎች ላይ ክህሎት ማስታጠቅ እና ማብቃት ይገባል ብለዋል።

የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መተባበር እና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም የሥራ ፈጠራ ገበያ ውድድር የበዛበት መሆኑን ጠቁመው የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ማጎልበትና ማበረታታት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለበርካታ ወጣቶች የክህሎት ሥልጠና በመስጠት ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ አስችሏል ነው ያሉት።

በዚህም ኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል አሰራር ስርዓት ተዘርግቶ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግባለች ብለዋል።

በእያንዳንዱ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከላት በማስፋፋት ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ምቹ ሥነ ምህዳር መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም