የደቡብ ንፍቀ ዓለም ለዓለም የጋራ ደህንነት እና ብልፅግና በትብብር መስራት አለበት - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 22/2017(ኢዜአ)፦ የደቡብ ንፍቀ ዓለም ለዓለም የጋራ ደህንነት እና ብልፅግና መረጋገጥ በትብብር መስራት እንዳለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ ሲካሄድ የነበረው የ2025 የመጀመሪያ የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተጠናቋል።

በስብሰባው ላይ "የደቡብ ንፍቀ ዓለም የባለ ብዝሃ ወገን ትብብርን በማጠናከር ያለው ሚና" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ውይይት ተካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የደቡቡ የዓለም ክፍል ገለልተኝነትን በማራመድ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መመስረቻ ቻርተር ውጤታማ በሆነ ሁኔታ እንዲተገበር በመስራት፣ ቅኝ ግዛትን በመታገልና ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

በሀገራት መካከል የወዳጅነት ትብብር እንዲኖር፣ የመልማት መብት እንዲከበር አልፎም ለዓለም ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ የተወጣውን ሚና አንስተዋል።

የዓለም የአስተዳደር ስርዓትን በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተነ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የደቡብ ንፍቀ ዓለም ትብብሩን የበለጠ በማጠናከር ለዓለም የጋራ ደህንነትና ብልፅግና መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የደቡቡ ዓለም ከተቀረው ዓለም ጋር ሲነጻጻር በግብርና፣ በኢነርጂ ልማት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ(አይሲቲ)፣ በመከላከያ፣ በንግድ እና ትስስር ያለውን አቅሞች እና እድሎች በመጠቀም ለደቡብ ንፍቀ ዓለም የጋራ ግብ እውን መሆን መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዓለም ላይ ያሉ ተፎካካሪ ፍላጎቶችን በአጋርነት መንፈስ ማስታረቅ እና ዓለም እያስተናገደቻቸው ያሉ ጉዳቶች እንዴት ምላሽ ያግኙ? ለሚሉ ጥያቄዎችም ጽኑ ቁርጠኝነት መያዝ እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት።

ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከስብሰባው ጎን ለጎን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ሁለቱ ሚኒስትሮች የሀገራቱን የሁለትዮሽ ትብብር በተለይም የኢኮኖሚ እና ንግድ ትስስር የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

ሀገራቱ በባለብዝሃ ወገን መድረኮች ያላቸውን መደበኛ ምክክሮች ለማጠናከርም ተስማምተዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሬም አል ሃሺሚ እና ከታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪስ ሳንጊያምቦንግሳ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የጋራ ፍላጎቶች በሆኑ መስኮች ላይ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን የማስፋት እና ትስስራቸውን የሚያጠናክሩ ኢኒሼቲቮችን መተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

ሚኒስትሩ ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ እና ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።

በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አጋር ሀገራት የሆኑት የቤላሩስ፣ ቦሊቪያ፣ ኩባ፣ ካዛኪስታን፣ ማሌዢያ፣ ናይጄሪያ፣ ታይላንድ፣ ኡዝቤኪስታንና ዩጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መሳተፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም