በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የባርሴሎና እና ኢንተር ሚላን ፍልሚያ - ኢዜአ አማርኛ
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የባርሴሎና እና ኢንተር ሚላን ፍልሚያ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፡- በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ባርሴሎና እና ኢንተር ሚላን ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ በካምፕኑ ስታዲየም ይካሄዳል።
በሩብ ፍጻሜው ባርሴሎና ቦሩሲያ ዶርትሙንድን፣ ኢንተር ሚላን ባየር ሙኒክን በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜው ደርሰዋል።
ሁለቱ ክለቦች በውድድሩ በግማሽ ፍጻሜ ደረጃ ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
እ.አ.አ 2009/10 ኢንተር ሚላን በደርሶ መልስ ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል።
ኔራዙሪዎቹ በፍጻሜው ባየር ሙኒክን በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳታቸው አይዘነጋም።
በአጠቃላይ ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ባርሴሎና 6 ጊዜ ሲያሸንፍ ኢንተር ሚላን ያሸነፈው 2 ጊዜ ብቻ ነው። 4 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
ባርሴሎና ሻምፒዮንስ ሊጉን 5 ጊዜ፣ ኢንተር ሚላን ደግሞ 3 ጊዜ ማንሳት ችለዋል።
በውድድሩ ለረጅም ጊዜ የካበተ ልምድ ያላቸው ሁለቱ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የ42 ዓመቱ ፈረንሳዊ ክሌመንት ቱርፓን ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።
ትናንት በሻምፒዮንስ ሊጉ በተደረገ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ፒኤስጂ ከሜዳው ውጪ አርሰናልን 1 ለ 0 አሸንፏል።