ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 21/2017(ኢዜአ)፡-
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የጋራ ስትራቴጂካዊ ፍላጎታቸውን ማዕከል በማድረግ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል።


 

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ እና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም ከስብሰባው ጎን ለጎን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ የተደረገው ከሚኒስቴሩ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊ ትሮይ ፊትሬል እና የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሐፊ ቪንሰንት ስፔራ ጋር ነው።

ሚኒስትሩ ለአሜሪካ ባለስልጣናቱ ስለ ኢትዮጵያ ጠንካራ በኢኮኖሚ የማደግ አቅም እና እድሎች፣ የዓለም ወቅታዊ ፈተናዎች እና የመንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ሂደት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሪፎርሙ ገበያውን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ እርምጃዎች መውሰዳቸውንና የንግድ ስራ ምቹነትን በማሻሻል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት የኢትዮጵያን የሪፎርም ስኬቶች አድንቀዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በጠንካራ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር እና አጠቃላይ የንግድ ስራ ምቹነትን በማሻሻል የፊስካል አቅምን ለመገንባት እየሰራች ያለው ስራ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ባለስልጣናቱ የሁለቱን ሀገራት ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እና አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል የፖሊሲ መጣጣም እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአሜሪካ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን እና የአሜሪካ የኤክስፖርት እና ኢምፖርት ባንክን ጨምሮ ከሀገሪቷ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትብብር በመፍጠር የፋይናንስ አማራጮች እና መሳሪያዎች እንድትጠቀም አበረታተዋል።

የአሜሪካ የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት እድሎችን የሚያሰፉበት የፋይናንስ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሁለቱ ወገኖች የአሜሪካ የግምጃ ቤት መስሪያ ቤት፣ ከአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቷ ተቋማት ከኢትዮጵያ አቻ ተቋማት ጋር ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

ተቋማቱ የኢትዮጵያ እና አሜሪካን የጋራ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ማዕከል ባደረገ መልኩ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ስለመገለጹ ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስትሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም