አማራ ክልል ከግብርናው ልማት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ምርታማነት እመርታዊ ስኬት እያስመዘገበ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
አማራ ክልል ከግብርናው ልማት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ምርታማነት እመርታዊ ስኬት እያስመዘገበ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ከግብርናው ልማት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ምርታማነትም እመርታዊ ስኬት እያስመዘገበ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ "የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን የወሎ ኮምቦልቻ ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪና የፋይናንስ ኤክስፖ በይፋ ከፍተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት ኤክስፖ የአማራ ክልል በግብርና ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ልማት ላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ኤክስፖው በአንድ በኩል ህግ የማስከበር ስራችንን በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ልማትን በማፋጠን አጠናክረን እንድንቀጥል መልዕክት የሰጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ሰላም የሚጸናው፣ የሚያድገው እና የሚዘልቀው በዋነኛነት ኢኮኖሚው ላይ ጠንክረን ስንሰራ ነው ብለዋል።
የኮምቦልቻ ከተማና አካባቢው ለባለሀብቶች ምቹ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለሀብቶች በኮምቦልቻ ከተማ በግብርና፣ በማዕድንና በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሰማሩ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።
ዛሬ የተከፈተው ኤክስፖም በአካባቢው ያለውን የመልማት ጸጋ ከአልሚዎች ጋር ለማገናኘት እድል የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ በበኩላቸው የኤክስፖው አላማ የአካባቢውን ጸጋ በመገንዘብ ወደ ሀብት ለመቀየር፣ እርስ በእርስ ለመማማር እና በጋራ ለማደግ ያለመ ነው ብለዋል።
ኮምቦልቻ የልማት ማዕከል እንዲሆን የፌደራል እና የክልሉ መንግስት የአሁን እና የወደፊቱን የከተማዋን እድገት የሚያረጋግጡ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እየተስፋፉ መሆናቸውን አመላክተዋል።