የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ አካታች የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ በቴክኖሎጂ ያደገችና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ አካታች የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡ 

ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 የአፍሪካ የትምህርት፣ አይሲቲ እና ክህሎት የሚኒስትሮች ስብሰባ "በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

የትምህርት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካን ብሬይን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አህጉራዊ ጉባኤ ነገ ይጠናቀቃል።


 

የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በሪፎርም፣ አቅም ግንባታ፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽግግር እንዲሁም ስትራቴጂካዊ ትብብር በመፍጠር የአፍሪካን መፃኢ ጊዜ ለመወሰን ያለመ ነው።

"ለኢኖቬሽን እና ትምህርት ሽግግር የዲጂታል ቴክኖሎጂን አቅም መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ የበለጸገችና በቴክኖሎጂ ያደገች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ሁነት ነው።

በአፍሪካ የዲጂታል ክህሎት እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አቅምን በማሳለጥ ልማትና እድገትን ለማቀላጠፍ ወጣቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂን ማስታጠቅ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ተሳትፎ የሚወሰነው በሚኖራቸው የቴክኖሎጂ አቅም መሆኑን በመግለጽ፤ አካታች ፖሊሲ በመተግበር የዲጂታል ሽግግሩን ማሳለጥ ይገባል ብለዋል፡፡


 

በአፍሪካ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የጋራ ጥረት ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሁሉንም የፈጠራ አቅሞች በመጠቀም ለወጣቶች ምቹ የዲጂታል ሥነ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግቧን ያሳካች አፍሪካን እውን ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ በትብብር ለመሥራት ቁርጠኝነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሒሳብ ትምህርቶች ለእድገት ወሳኝ መሆናቸውን በመገንዘብ ያልተቋረጠ ጥረት እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል።

በመንግስትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ጥረት የስታርታፕ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ኢትዮጵያ ማዕከል እየሆነች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በኢንዱስትሪዎች እና ትምህርት ተቋማት መካከል ትብብርን በማዳበር ለስራ ፈጣሪዎች ምቹ ከባቢ እንዲኖር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የበለጸገች አፍሪካውን እውን ለማድረግ ሁሉንም የኢኖቬሽን አቅም በመጠቀም ለችግሮቻችን መፍትሔ ማበጀት ይገባል ነው ያሉት፡፡


 

የደቡብ ሱዳን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ማይክል ማኩይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት እንደ ኤሌክትሪክ ሀይልና የኢንተርኔት አገልግሎት የሚጠይቅ በመሆኑ ዘርፉን በሚገባ ማሳደግ አልተቻለም ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2012 የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፖሊሲ በማውጣት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2024 ወጣቶችን መሰረተ ያደረገ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ በትክክለኛ ሂደት ላይ ነን ብለዋል፡፡


 

የማላዊ ኢንፎርሜሽንና ዲጂታላይዜሽን ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ዳይሬክተር አርቸር ቺፔንዳ በበኩላቸው፤ ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ ራዕይ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ማላዊ ከሁሉት ዓመት በፊት የማላዊ ብሔራዊ ዲጂታላይዜሽን ፖሊሲ በማጽደቅ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ም ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ስርዓቱን በማቀላጠፍ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ንግድን ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም