መንግስት ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እያደረገ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው - የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እያደረገ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው - የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እያደረገ ባለው ተግባር መደነቃቸውን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ገለጹ።
ገዥውን ፓርቲ ብልጽግናን ጨምሮ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በይፋ የተመረቀውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጎብኝተዋል።
ለፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች ስለ ማዕከሉ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
በአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከሉ 12 የመንግስት ተቋማት 41 አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆኑ ተጠቅሷል።
እንዲሁም አገልግሎቱ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ግልፅ በመሆኑ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን የሚያስቀር መሆኑም ነው የተመለከተው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት መንግስት ዜጎች በተደጋጋሚ ሲያነሱት ለቆዩት የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት የሄደበትን እርቀት አድንቀዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ የሴቶች አደረጃጀት ኃላፊ ትዕግስት አሰፋ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ መንግስት ተቋማት ሲሄዱ የሚያጋጥሟቸውን የቢሮክራሲ አሰራሮች አስታውሰዋል።
ይሁንና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከጠበቁት በላይ እንዳገኙት አመልክተው፤ የበርካታ ዜጎችን የአገልግሎት እርካታ የሚጨምር መሆኑን ገልጸዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተመለከቱት ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ መደመማቸውንም ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ዜጎች ካለምንም እንግልት የመጡበትን ዓላማ ፈጽመው የሚመለሱበት መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሰለሞን ታፈሰ ናቸው።
መሶብ ሀገር ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባትና የዜጎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ፍላጎት ለማርካት የተሄደበትን ርቀት ያሳያል ብለዋል።
የወሎ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢማም መሃመድ በበኩላቸው፤ በሰለጠኑት ሀገራት ያዩትን አገልግሎት መሶብ ውስጥ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
አንድ ጉዳይ ለመጨረስ ይወስድ የነበረውን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብ ከብልሹ አሰራር የጸዳ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል።