ቀጥታ፡

አምራች ኢንዱስትሪንና ኢንቨስትመንትን የማስፋትና ሰላም የማፅናት ተግባርን አጠናክረን እንቀጥላለን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ አምራች ኢንዱስትሪንና ኢንቨስትመንትን የማስፋትና ሰላም የማፅናት ተግባርን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ "ሰላም የኢንቨስትመንት ፓስፖርት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ወሎ ኮምቦልቻ ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪና የፋይናንስ ኤክስፖ በይፋ ከፍተዋል።

በመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያ የማይመጥናትን የድህነትና የኋላ ቀርነት ጉዞ ላይ መቆየቷን አውስተዋል።

ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያን ሰንኮፎች የመንቀል፣ ከድህነት ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር ፀጋዋን የመለየትና የመጠቀም ሥራዎችን በማከናወን ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ታምርት የሚለው ሀገራዊ ንቅናቄ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የኢትዮጵያን ማንሰራራት እያበሰረ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ታምርት በአንድ በኩል ከውጭ ተመርተው የሚመጡ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ዓላማ እንዳለው አመልክተው፤ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የማምረት አቅሟን በማሳደግ በዓለም ገበያ ያላትን ተደራሽነት ማስፋት መሆኑንም ገልጸዋል።

አምራችነትና ሰላም እጅግ የተሳሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ተዘዋውረን የተመለከትናቸው ደሴና ኮምቦልቻ ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥተዋል ነው ያሉት።

የአካባቢው ህዝብ ማን እና ምን እንደሚጠቅመው በመለየት ግጭት ጠማቂዎችን በመጠየፍ፣ ሰላምን ጠብቆ ለዕድገትና ብልፅግና እየተጋ መሆኑንም ተመልክተናል ብለዋል።

ጊዜው የብልፅግና እንጂ የግጭት አይደለም ያሉት አቶ ተመስገን፤ የይቅርታና የመደመር፣ በሀገራዊ አጀንዳ ላይ በመመካከር ልዩነቶችን በሰላም የመፍታት በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል።

መንግሥት ሁል ጊዜም ለሰላም በሩ ክፍት መሆኑን ጠቅሰው፤ የትኛውም ልዩነት ያለው ኃይል ከግጭት ይልቅ የሰላም አማራጭን በመከተል ለሀገርና ለህዝብ ሰላምና ልማት መስራት ይገባል ብለዋል።


 

ያለንበት ዘመን በእውቀት ሀገርን ወደ ላቀ ከፍታ የማሻገር በመሆኑ በትጋት መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ጊዜው የእርሻ እንጂ የረብሻ፣ የማምረቻ እንጂ የመሻኮቻ አይደለም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንዳንድ ግጭት ጠማቂዎች ከዓላማ ቢስና የሌሎችን ዕኩይ አላማ ለማስፈጸም ከሰላምና ከልማት ተቃራኒ መቆማቸውንም አንስተዋል።

ህዝብ ልማት የሚያፋጥንለትንና ሰላምን የሚጠብቅን አካል በመደገፍ በትጋት ለአካባቢው ለውጥ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል።

ለዕድገትና ለሰላም ደንቃራ የሆኑ ኃይሎች የመንግሥትን ጥሪ በመቀበል በይቅርታ ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን መንግሥት የሰላም ጥሪን ባለመቀበል የህዝቡን ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፉ አካላት ላይ የሚወስደውን ህግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የወሎ ኮምቦልቻ ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪና ፋይናንስ ኤክስፖ እስከ ሚያዚያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ከ200 በላይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፣ የፋይናንስ እንዲሁም የልህቀት ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን ለዕይታና ለግብይት አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም