አሰባሳቢ እና ገዥ ትርክትን ለማስረጽ በሚደረገው ጥረት የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን ማጣናከር ይጠበቅባቸዋል - ማዕከሉ - ኢዜአ አማርኛ
አሰባሳቢ እና ገዥ ትርክትን ለማስረጽ በሚደረገው ጥረት የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን ማጣናከር ይጠበቅባቸዋል - ማዕከሉ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አሰባሳቢ እና ገዥ ትርክትን ለማስረጽ በሚደረገው ጥረት የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን ማጣናከር እንደሚጠበቅባቸው የሕገ መንግሥትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ገለጸ።
ማዕከሉ "ፌደራሊዝም፣ ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም፣ ሀገረ መንግሥት ግንባታና የትምህርት ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ለትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ ባለሙያዎችና መምህራን የአሰልጣኞች ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
በሥልጠናው ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ሥልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝምና ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሳካት ለሀገር ዘላቂ ሠላምና እድገት መረጋገጥ ቁልፍ ሚና አለው።
በመሆኑም በትምህርት ተቋማት በኩል ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት ጥናት መደረጉን ጠቅሰው፤ በጥናቱ መሰረት የትምህርት ማኀበረሰቡን ወደ ማሰልጠን መገባቱን አብራርተዋል።
ተሳታፊዎችም በሥልጠና ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት በትምህርት ተቋማት ብሎም ማህበረሰቡን በማስገንዘብ የፌደራሊዝም ጽንሰ ሀሳብ እንዲሰርጽ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የፌደራሊዝም ጉዳይ በትምህርት ተቋማት በሥርዓተ ትምህርት ተካትተው ለተማሪዎች በአግባቡ እንዲሰጡ ማዕከሉ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
በፌደሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዘውዴ ደምሴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አሰባሳቢ እና ገዥ ትርክትን ለማስረጽ በሚደረገው ጥረት የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተማሪዎች ዘንድ የአንድነት እሴት እንዲያብብ በክበባት ሀገራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ሀሳቦች እንዲቀነቀኑ፣ ሕገ መንግሥትና ፌደራሊዝም ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተሻለ ታደሰ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ያለኝን ግንዛቤ በማስፋት ለሌሎች እንዳካፍል ትልቅ ስንቅ ይሆነኛል ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ ገመቺስ ኦላና በበኩላቸው መሰል የአቅም ግንባታ መርሃ ግብሮች ዜጎች ፌደራሊዝምን በተሻለ መልኩ ተረድተው እንዲተገብሩት አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።