በህፃናት የቀዳማይ ልጅነት አስተዳደግ ላይ የሚታዩ አበረታች ጅምሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ በህፃናት የቀዳማይ ልጅነት አስተዳደግ ላይ የሚታዩ አበረታች ጅምሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የስፖርት እና የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ አስገነዘቡ።

በድሬዳዋ በህፃናት የቀዳማይ ልጅነት አስተዳደግ በተዘጋጀ ጥናት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩም ዕድሜያቸው ከስድስት ዓመት በታች ህፃናት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


 

በመድረኩ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የስፖርትና የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ፤ የመድረኩ አላማ የቀዳማይ ልጅነት ዘመን ላይ በጤና፣ በስርዓተ ምግብ፣ በሁለንተናዊ እንክብካቤ፣ በትምህርትና በደህንነታቸው ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።

በህፃናት የቀዳማይ ልጅነት አስተዳደግ ላይ እየታዩ ያሉት አበረታች ጅምሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ አጠቃላይ ክልሎች ለተሻለ ስራ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ጥናቱ በልጆች ዕድገትና ትምህርት ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ህፃናት በተሻለ መልኩ እንክብካቤ ተደርጎላቸው እንዲያድጉ ከወዲሁ መስራት የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፤ በህፃናት የቀዳማይ ልጅነት ዘመን የልጆችን እድገት የተሻለ ለማድረግ በቅንጀት የምንሰራቸው ስራዎች ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ትርጉም ያላቸው ናቸው ብለዋል።

በሁሉም ረገድ አሁን ላይ ለህፃናት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


 

የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ስራ አስፈፃሚ ዶክተር መሠረት ዘላለም፤ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ከተቋቋመ ጀምሮ በቀዳማይ ልጅነት ላይ ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን አንስተዋል።

የአዲስ አበባን ተሞክሮ በማስፋት በሁሉም አካባቢዎች በህፃናት ቀዳማይ የልጅነት አስተዳደግ ላይ የተደመረ ውጤት ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ከማዕከሉ እንቅስቃሴ ባለፈ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና አጠቃላይ ዜጎች የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም