ለባህርዳር ከተማ ሰላም መጠበቅ የነቃ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - የከተማዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለባህርዳር ከተማ ሰላም መጠበቅ የነቃ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - የከተማዋ ነዋሪዎች

ባህርዳር ፤ ሚያዚያ 21/2017(ኢዜአ)፦ ለባህርዳር ከተማ ሰላም መረጋገጥ በባለቤትነት እያደረግነው ያለው ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ቀበሌዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉባቸው ህዝባዊ መድረኮች ዛሬ ተካሄደዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ለከተማዋ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መረጋገጥ በባለቤትነት መንፈስ እያከናወኗቸው ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በከተማው የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሃብታሙ ገብረእግዚአብሄር፤ የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎና አንድነት ካለ የማይሳካ ስራ እና እቅድ እንደሌለ አንስተዋል።
የባህር ዳር ከተማን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የፀጥታ ሃይሉ ጠንካራ ስራ እንዳለ ቢሆንም የነዋሪውም ተሳትፎና ሚና ታክሎበት የተገኘ ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የከተማዋን ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ በማኖር ሁለንተናዊ ልማትና ሀገራዊ እድገትን የማስቀጠል ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በተለይም የሰላም ማስጠበቅ ስራ ለአንድ አካል ብቻ የማይተው በመሆኑ በባለቤትነት የምንሰራው የጋራ ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የሁሉም ነገር መሰረቱ ከምንም በላይ ሰላም በመሆኑ ከመንግስትና ከፀጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ቄስ ገብረመድህን አምሳሉ፤ የእምነት ተቋማትና የኃይማኖት አባቶች የመጀመሪያ ተግባር ለሰው ልጆች ሰላምን መሻት መልካምነትን ማብዛት መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ለሀገር ሰላም እና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆን አለብን ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በተለይም ወላጆች ልጆችን የመምከርና ከጥፋት እንዲርቁ የማድረግ ኃላፊነት አለባችው ሲሉም መክረዋል።
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ አበጀ አበበ፤ በባህር ዳር ከተማ ሰላምን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ በልማት ስራዎች ለተከናወኑት ተግባራት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የልማት ስራዎች ከግብ ደርሰው ባህርዳር ለነዋሪዎቿ እና ለቱሪስቶች ምቹና ተመራጭ ሆና እንድትቀጥል ሰላማችንን ማፅናት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በጣና ክፍለ ከተማ የተካሄደውን ህዝባዊ የውይይት መድረክ የመሩት የከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለሚካኤል አርዓያ፤ የህዝባዊ ውይይቱ ዓላማ እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም ለማጽናት መሆኑን አንስተዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በቅርበት በመስራት ወንጀለኞችን በማጋለጥና በፅንፈኝነት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመቆጣጠር በከተማዋ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋፅኦ አድርገዋል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ ቀበሌዎችም ተመሳሳይ የህዝብ መድረኮችን በማካሄድ ሰላምን የማስጠበቅ ጉዳይ የጋራ ስራ ሆኖ እንዲቀጥል መግባባት ላይ ተደርሷል።