ምክር ቤቱ የክልሉን ሕዝቦች መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል - የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የክልሉን ሕዝቦች መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል - የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት
ቴፒ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት የክልሉን ሕዝብ መብትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገለፀ።
የምክር ቤቱ ሦስተኛ ዓመት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ በቴፒ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ መቱ አኩ በወቅቱ እንዳሉት ምክር ቤቱ የክልሉን ሕዝቦች መብትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
የለውጡን መልካም ዕድል በመጠቀም በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች መብትና ጥቅም እንዲረጋገጥ፣ በቋንቋ ልማትና በታሪክ ስነዳ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባለፉት 9 ወራት በክልሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል፣ የሰላም እሴት ግንባታና የሀገር በቀል እውቀት ልማት ላይ ያተኮሩ ተግባራት መከናወናቸውን አመላክተዋል።
የግጭት አፈታት እሴትን ለማጎልበትም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና መሰጠቱን የገለፁት ደግሞ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሰለ ከበደ ናቸው።
የስድስት ብሔረሰቦችን ባህላዊ እሴቶች ማጥናት የሚያስችል ሂደት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ግጭት እንዳይከሰት መከላከል የሚያስችል ውይይት መደረጉን እንዲሁም ችግሮቹ እየተቀረፉ መምጣታቸውንና በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀራረብ በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።