የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው

ደሴ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ በደሴ ከተማ የሚገኘው የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የዓይን ሞራ ግርዶሽ ላለባቸው ሰዎች ነፃ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በዘመቻ እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።
የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ዳዊት ሁሴን እንደገለጹት ሆስፒታሉ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የነፃ ቀዶ ህክምና አገልግሎቱ ከሁለት ሺህ በላይ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ያለባቸው ሰዎችን ለማከም ማቀዱን ጠቁመዋል።
በዚህም አገልግሎቱ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ወሎ፣ በዋግኽምራ ብሔረሰብ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ፣ በሰሜን ሸዋ ዞኖችና ከአፋር ክልል ለሚመጡ ህክምና ፈላጊዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
በአገልግሎቱ ነጻ የዓይን ቆብ ቀዶ ህክምና ከመስጠት ባሻገር ለመታከም ለሚመጡ ተገልጋዮች የትራንስፖርትና የምግብ ወጪዎች እንደሚሸፈንላቸው ጠቁመው ለእያንዳንዱ ታካሚ ከ15 ሺህ ብር በላይ በጀት እንደተያዘም ተናግረዋል።
የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል ሃላፊና የነጻ ህክምና አገልግሎቱ አስተባባሪ አቶ እንዳልክ ያረጋል በበኩላቸው አብዛኛውን ጊዜ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በዕድሜ መግፋት የሚከሰት ነው ብለዋል።
ሕክምናው ኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው ከሁለት ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ መጀመሩን ገልፀዋል።
የነጻ ቀዶ ህክምና አገልግሎቱ በተጀመረበት ዕለትም 366 ታካሚዎችን ማስተናገድ መቻሉን ገልጸው በዛሬው ዕለት ደግሞ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎቱ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።
በህክምናው የሆስፒታሉ ስምንት የዘርፉ ስፔሻሊስት ዶክተሮችን ጨምሮ 120 የዓይን ሐኪሞችና ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለፉት ዓመታት ከ22ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የዓይን ሞራ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።