መንግስት በመንገድ መሠረተ ልማቶች ተደራሽነት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በመንገድ መሠረተ ልማቶች ተደራሽነት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ
ቦንጋ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት በመንገድ መሠረተ ልማቶች ፍትሀዊነት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የዲሪ-ማሻ አስፋልት መንገድ የምዕራፍ አንድ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በዚህ ውቅት እንደገለጹት መንግስት መሠረተ ልማቶች ፍትሀዊነት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
የመንገዱ መገንባት ከተማን ከገጠሩ ጋር እንደሚያስተሳስር ገልጸው፣ ይህም የትምህርትና የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በተለይ የመንገድ መሰረተ ልማትን ተደራሽነት ማረጋገጥ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን አልምቶ ለሀገር ብልፀግና ለማዋል ተጨማሪ አቅም ይሆናል ነው ያሉት።
የግንባታ ሥራው ዳግም ለተጀመረው መንገድ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመው፣ ሥራው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ሀብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው፣ በክልሉ ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት እንዲኖር ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
ዛሬ ግንባታው ዳግም የተጀመረውና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የዲሪ ማሻ አስፋልት መንገድ ግንባታ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመንገዱ መገንባት የወረዳዎቹን የእንስሳትና የግብርና ምርቶች በፍጥነት ወደ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አለማየሁ አየለ(ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ብለዋል።
መሰረተ ልማትን ተደራሽ የማድረጉ አካል አንዱ የሆነው የዲሪ-ማሻ አስፋልት መንገድ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተገነቡ ካሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የመንገዱ ግንባታ በ2010ዓ.ም ከተጀመረ በኋላ መቋረጡን አስታውሰው ዛሬ ዳግም የግንባታ ሥራው መጀመሩን ተናግረዋል።
የመንገድ ግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነውና ከጊምቦ-ቆንዳ የሚደርሰው የ61 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ቀደም ሲል በኮንትራክትር የአቅም ውስንነት ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን አስረድተዋል።
የመንገዱን ግንባታ ለማስፈጸም ከ6 ቢሊዮን 281 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙንና ሥራውን በሦስት ዓመት ከአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።