መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የብልፅግና እሳቤዎች በተግባር የሚታዩበት ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የብልፅግና እሳቤዎች በተግባር የሚታዩበት ነው - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የብልፅግና መሰረታዊ እሳቤዎች በተግባር የሚታዩበት መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።
ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የመደመር እሳቤ ከተናጠል ሥራ ይልቅ በጋራ የተሻለ ነገር ማሳካት፣ በተናበበና በተቀናጀ መልኩ መስራት ውጤቱ ያማረ መሆኑን ማዕከሉ ማሳያ ነው።
የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ሰው ተኮር መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ሁሉንም ዜጋ በእኩልነትና በፍትሃዊነት የሚያገለግል ሀገራዊ ተቋም ነው ብለዋል።
የመንግስት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የታገዙ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እንዲሁም የጥራት ደረጃቸውን ያሟሉ እንዲሆኑ ሰራተኞችን ከማሰልጠን ባለፈ የተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን መደረጉን ገልጸዋል።
በማዕከሉ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት የሚችሉ ባለሙያዎች መኖራቸው መንግስት ለተቋማት ግንባታ የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።