የእንስሳት ጤና እና ደህንነት አዋጅ በዘርፉ የተያዘውን ግብ ማሳካት የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት ጤና እና ደህንነት አዋጅ በዘርፉ የተያዘውን ግብ ማሳካት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፡- የእንስሳት ጤና እና ደህንነት አዋጅ በሀገሪቱ በዘርፉ የተያዘውን ግብ ማሳካት የሚያስችል መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 27ኛ መደበኛ ስብሰባ የእንስሳት ጤና እና ደህንነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ረቂቅ አዋጁ እየተንሰራፋ የመጣውን ከሰው ወደ እንስሳ እና ከእንስሳ ወደ ሰው ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ወደ አገር የሚገቡትንም ሆነ የሚወጡትን እንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት የዓለም አቀፉን የእንስሳት ጤና ድርጅት አሰራርና ሕግ በተከተለ መልኩ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከፍ በማድረግ የባለሞያዎችን እውቀትና ክህሎት በማጎልበት ተጠያቂነትን በተላበሰ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ ሥርዓት የሚያስቀምጥ መሆኑን አንስተዋል።
ወቅቱን የጠበቀ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን የዳሰሰ የሕግ ማዕቀፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅቱ እንዳሉት አዋጁ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዋጁ የተቀመጡ የቅጣት ድንጋጌዎች አስተማሪ መሆን እንዳለባቸው እና የቅጣት እርከኖቹን በተመለከተ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ አዋጁ የህግ ክፍተት እንዳይኖረው ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ ለዘርፉ ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
የእንስሳት ጤና እና ደህንነት አዋጅ በዘርፉ እንደሀገር የተያዘውን ግብ ማሳካት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
ምክርቤቱም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ከተመለከተ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
ምክር ቤቱ በቀጣይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለምክር ቤቱ የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ አመራሮችን ለመሰየም የሚያስችል የውሳኔ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ እና አቶ መለሰ መና ለአመራርነት ቀርበዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የቀረቡት አመራሮች በትምህርት ዝግጅት እንዲሁም ባላቸው የስራ ልምድ ቋሚ ኮሚቴዎቹን በብቃት መምራት እንደሚችሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዚህም መሰረት ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶን የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም አቶ መለሰ መናን ደግሞ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አድርጎ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡