በመከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት የገንዘብ ድጋፍ በሰቆጣ ከተማ የህዝብ ዲጅታል ቤተ መፃሕፍት ግንባታ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በመከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት የገንዘብ ድጋፍ በሰቆጣ ከተማ የህዝብ ዲጅታል ቤተ መፃሕፍት ግንባታ ተጀመረ

ሰቆጣ ፤ ሚያዚያ 21/2017(ኢዜአ)፡- በመከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት የገንዘብ ድጋፍ በሰቆጣ ከተማ የህዝብ ዲጅታል ቤተ መፃሕፍት ግንባታ መጀመሩን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ገለጸ።
የዕዙ አባላት ከዚህ ቀደም በአስተዳደሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ጨምሮ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ሲከናውኑ መቆየታቸውንም ታውቋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይሉ ግርማይ፤ በዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት የገንዘብ ድጋፍ በሰቆጣ ከተማ የህዝብ ዲጅታል ቤተ መፃሕፍት ግንባታ በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል።
የዕዙ አባላት ቀደም ሲል ከ60 ሚሊዮን ብር በማዋጣት በተለይም የአካባቢው ወጣቶች የዲጅታል ቤተ መጽሃፍት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሰብ ለዚህ ዓላማ መነሳሳታቸውን አስታውሰዋል።
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ባለፈ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወንና በማገዝ ህዝባዊነቱን በተግባር የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።
የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት ገንዘብ በማዋጣት በሰቆጣ ከተማ የህዝብ ዲጅታል ቤተ መፃሕፍት ግንባታ እንዲከናወን ማድረጋቸውም የዚሁ መልካም ተግባር ማሳያ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ቤተ መፃሕፍት ግንባታው በስድስት ወራት የሚጠናቀቅ ሲሆን በተያዘለት ጊዜ ለመጨረስ አስተዳደሩ ሌት ተቀን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ፤ የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ እያኖሩት ላለው አሻራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመሆኑም በዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት የገንዘብ መዋጮ ግንባታው የተጀመረው ቤተ መፅሃፍት በግንባታ ተቋራጩ በጥራትና በፍጥነት እንዲከናወን የቅርብ ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።
ግንባታውን የሚያከናውነው የአስፋው ቸኮለ ጠቅላላ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሃይለማርያም አስፋው፤ የቤተ መፃሕፍቱን ግንባታ በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በግንባታ ሂደቱም እስከ 300 ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በልምድና እውቀት ሽግግር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።
የቤተ መጽሃፍቱ የመሰረት ድንጋይ የዳሉል ማዕከላዊ ዕዝ ከፍተኛ መኮንኖች በተገኙበት የተቀመጠ መሆኑ ታወቋል።