በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተደረገልን ድጋፍ ፈጥነን ወደ ማምረት እንድንሸጋገር አስችሎናል - ባለሃብቶች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተደረገልን ድጋፍ ፈጥነን ወደ ማምረት እንድንሸጋገር አስችሎናል - ባለሃብቶች
ደሴ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተደረገልን ድጋፍ ፈጥነን ወደ ማምረት በመሸጋገር በገበያ ማረጋጋት ላይ የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ አስችሎናል ሲሉ በኮምቦልቻ ከተማ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ገለፁ።
የወሎ ኮምቦልቻ ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪና የፋይናንስ ኤክስፖን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙ የከተማዋ ባለሃብቶች እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተደረገላቸው ድጋፍ ፈጥነው ወደ ማምረት በመግባት ገበያን በማረጋጋቱ በኩል የበኩላቸውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ የዱቄት ፋብሪካ ባለቤት የሆኑት አቶ ከድር አሊ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት በተደረገላቸው ጠንካራ ድጋፍ የፋብሪካ ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ማምረት ገብተዋል።
በቀን ከ400 ኩንታል በላይ ዱቄት በማምረት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን በማረጋጋት በኩል አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ለ114 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደቻሉ ገልጸው መንግስት እያደረገ ያለው ሁለተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ሌላው ባለሃብት አቶ ይመር አሊ ከ770 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ካፒታል በተቀናጀ አግሮ ኢንዱሰትሪ ዘርፍ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤሌክትሪክን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማት ችግሮች በመቃለላቸው ምርታማነታቸውን በእጥፍ አሳድገው የዋጋ ንረትን ተፅዕኖ በመቀነስ በኩል አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በከተማው የኢንቨስትመንት ዘርፉ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።
በከተማዋ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች 73 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ተኪ ምርት በማምረትና ከ34 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በከተማው በግንባታ ላይ የሚገኙ 110 ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች ወደ ምርት እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው አስተዳደሩም 11ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድና 6 ድልድዮችን በመገንባት ዘርፉን ለማነቃቃት እየሰራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን ለማቃለል እንዳስቻለ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሬት በማቅረብ፣ የብድርና የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማቀላጠፍ ተኪና የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ አበረታች ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው የኢንቨስትመንት ዘርፉን በመደገፍ ተኪ ምርት ከማምረት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ እንዲያመጣና ገበያውን እንዲያረጋጋ እየተሰራ ነው ብለዋል።