በክልሉ በሚቀጥሉት አራት ወራት 50 ሺህ ወጣቶችን በኢትዮ ኮደርስ ለማሰልጠን ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በሚቀጥሉት አራት ወራት 50 ሺህ ወጣቶችን በኢትዮ ኮደርስ ለማሰልጠን ይሰራል

ቦንጋ፤ ሚያዝያ 21/2017 (ኢዜአ)፡-በቀጣይ አራት ወራት 50 ሺህ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለመስጠት እንደሚሰራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ ገለፁ።
ቢሮው ለክልሉ ወጣት ክንፍ አመራሮች ስልጠናውን በማስመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ኢንሼቲቮች ተቀርፀው እየተተገበሩ ይገኛሉ።
በዲጅታል ኢኮኖሚ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግም የ5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለክልሉ ወጣቶች በመስጠት የዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ለመውሰድ ከተመዘገቡ ከ11ሺህ በላይ ወጣቶች መካከል ከ8 ሺህ 400 በላይ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ስልጠና ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የግንዛቤ እጥረት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የኢንተርኔት ችግርና ቅንጅታዊ አሰራር አለመጠናከር በዓመቱ ለማሰልጠን በተያዘው ዕቅድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አመልክተዋል።
በቀጣይ አራት ወራት የግንዛቤ ችግሩን በመፍታትና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር 50ሺህ ወጣቶችን መዝግቦ ለማሰልጠን በንቅናቄ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
በመድረኩ የተገኘው የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወጣት ሰይድ ኢብራሂም በበኩሉ እንደገለጸው፣ እንደሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተሰላፊና ተጠቃሚ መሆን አለበት።
የተጀመረው የ5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናም ለወጣቱ ትልቅ እድል ይዞ በመምጣቱ የወጣት ክንፍ አመራሮች ለስልጠናው መሳካት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የቦንጋ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወጣት ታሪኩ አለማየሁ፣ ስልጠናው ያለውን ፋይዳ ለወጣቶች በማስገንዘብ የዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግሯል።
በመድረኩ ላይ የፌደራል ወጣት ክንፍ አባላት፣ የክልል ሥራ አስፈፃሚ፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር የወጣት ክንፍ አመራሮች ተሳትፈዋል።