ቀጥታ፡

በዞኑ አረቅጥ ከተማ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ተደረጉ

ወልቂጤ፣ሚያዝያ 21/2017  (ኢዜአ)፡- በጉራጌ ዞን በአረቅጥ ከተማ አስተዳደር ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ተገለፀ።

አረቅጥ ከተማ አስተዳደር በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ እድገትን እያስመዘገበ ያለ ከተማ መሆኑም ተገልጿል። 

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ የማስፈፀም አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ተወካይ እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስታንዳርዳይዜሽን ዳይሬክተር ተፈራ ስሜ (ዶ/ር) እንደገለፁት ከተማው ከተመሰረተ 3 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ  ቢሆንም ለኑሮ ምቹ እና ለአይን ሳቢ ማድረግ ተችሏል።

በዚህም ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የመንገድ ከፈታና ጥርጊያ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና የዲች ግንባታ ስራዎች፣ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ማእከል፣ ለከተማ ግብርና አገልገሎት መሰረተ ልማት እና የቢሮ ግንባታ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ብለዋል።


 

በተጨማሪም የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቢሮዎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የልማት ስራዎቹን ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑ መሆናቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ ተገልጋይ ተኮር ሆኖ የተገነባው ማዕከልም ሁሉም ግብዓቶች እንደተሟሉለትም አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ  በበኩላቸው በአረቅጥ ከተማ የተከናወኑት የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የዲች ስራ፣ የመኖሪያ ቤቶች ቦታ አቅርቦትና የመብራት ዝርጋታ ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል። 


 

በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ከተማዋን ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን በማድረግ ደረጃቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስቡ ባለሃብቶችን ለመሳብ ያስችላል ብለዋል ።

የተገልጋይ ፍላጎትን ያገናዘበ የአንድ ማእከል አገልግሎት ማዕከልም ዘመናዊ የገቢ አሰባሰብ፣ የመሬት አስተዳደር፣ የኮንስትራክሽን እና የካዳስተር አሰራርን በመዘርጋት ዲጂታላይዝድ የሆነ አገልግሎትን ለመስጠት እንደሚያስችልም ገልፀዋል። 

የአረቅጥ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መንግስቱ ሹሜ በከተማው ደረጃውን የጠበቀ 4 ነጥብ 5 ኪ/ሜ የገረጋንቲ መንገድ፣ 3 ነጥብ 5 ኪ/ሜ የኮብልስቶን ንጣፍ፣ የ10 ነጥብ 5 ኪ/ሜ ዲች እንዲሁም የውሃ እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል። 

የልማት ስራዎቹም ለ2 ሺህ 500 ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ገልፀው ከ20 ኪ/ሜ በላይ የመንገድ ከፈታና ጠረጋ፣ የዲችና የገረጋንቲ ንጣፍ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

ለዚህም ህብረተሰቡ በጉልበት ካደረገው ድጋፍ ባሻገር 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በማዋጣት ለኤሌክትሪክ ዝርጋታ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል። 

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ሀጂ ከማል አህመድ በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የነዋሪውን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ  አልሚ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። 

ከተማዋን ሳቢና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አይሻ  ረሺድ በከተማው የመብራት፣ የመንገድ፣ የከተማ ግብርና እና ጉዳይ ለማስፈጸም የሚያስችሉ ማእከላት በመገንባታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም