በክልሉ የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ስርዓትን የመዘርጋቱ ተግባር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ስርዓትን የመዘርጋቱ ተግባር ይጠናከራል

ደብረ ብርሃን፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ለማሻሻል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ስርዓት የመዘርጋቱ ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ጤና ቢሮ የተዘጋጀ የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማና በጤናው ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ጉብኝት በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በጉብኝቱ ላይ እንደገለጹት በክልሉ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ለማሻሻል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ስርዓት የመዘርጋቱ ተግባር በትኩረት እየተከናወነ ነው።
በጤናው ዘርፍ ቴክኖሎጂን በማበልጸግና በመጠቀም የሚሰጡ አገልግሎቶችና አሰራሮችን ቀልጣፋ በማድረግ በህብረተሰቡ ዘንድ እርካታ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ለውጤታማነቱም በክልል ደረጃ የሚተገበሩ ከወረቀት ንክኪ ነጻ አገልግሎቶችን ጨምሮ አዳዲስ ኢንሼቲቮች መጀመራቸውን አስረድተዋል።
አገልግሎቱን ለማዘመን በተሰራው ስራ በ25 ጤና ጣቢያዎች ብቁ ሙያተኞችንና መሳሪያዎችን በማሟላት የቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
የህክምና መሳሪያዎች፣ መድኃኒትና ሌሎች ግብዓቶች ላይ የሚስተዋለውን እጥረት በቴክኖሎጂ በመታገዝ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ችግሩ ተለይቶ እንደሚፈታም ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው በከተማዋ እየተስፋፉ የመጡትን የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ዘርፎችን የሚመጥን ጽዱ፣ ውብና ምቹ የጤና ተቋማትን ለመፍጠር መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።