በፈጠራ ስራ ችግር ፈቺ ውጤቶችን በማበርከት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦መንግስት ለአገር ውስጥ ምርት የሰጠው ትኩረት ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን በማበርከት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እድል ፈጥሯል ሲሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የፈጠራ ስራ ባለሙያዎችና አምራቾች ገለጹ።

መንግስት የአገር ውስጥ ምርትን በማበረታታት ምርትና ምርታማነትን ለማስፋት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአገር ውስጥ ምርቶችን በስፋትም በጥራትም በማምረት ከአገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እድል ማመቻቸት ተጠቃሽ ነው።

እንዲሁም የስታርት አፖችን አቅም ከማጎልበትና ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የፈጠራ ስራዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ምቹ እድል መፍጠሩ አይዘነጋም።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የፈጠራ ባለቤቶችና የአገር ውስጥ አምራቾች እንደገለጹት፥ በአሁኑ ወቅት በመንግስት በኩል ዘርፉን ለማገዝ የሚደረጉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው።

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች በጋራ በመሆን የሰሩት የእንሰት ምርት ማቀነባበሪያ የፈጠራ ስራ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በላይ ጣፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት ቴክኖሎጂው እንሰትን በቀላሉ ወደ ምግብነት ለመቀየር የሚያግዝ ነው።

ቆጮ በባህላዊ የአዘገጃጀት ዘዴ ሲመረት ከፍተኛ የሰው ጉልበትን የሚጠይቅና የምርት ብክነትን የሚያስከትል ከመሆኑ ባሻገር ለምግብነት ለማዋል ከሶስት እስከ አራት ወር ጊዜ እንደሚወስድ ገልጸዋል።

በምርምር የበለጸገው ቴክኖሎጂ ምርቱ በጥራት እንዲመረት ከማድረጉ በተጨማሪ ጊዜውን ወደ ሰባት ቀን ማሳጠር የቻለ ነው።

በዚህም ቆጮን ከአገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ አስፈላጊው ሂደት በመጠናቀቁ በቅርቡ ምርቱ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል።

የዳፍ ቴክ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ደነቀው በሪሁን ድርጅታቸው የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችንና ቴክኖሎጂዎችን እያመረተ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የውሃና የመብራት ቆጣሪን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተሰራው የፈጠራ ስራ ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመምራትና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂው በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ በተደረገባቸው የመንግስት ተቋማት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱ በመታመኑ በአእምሯዊ ንብረት መመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡

የየትም ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኢክራም አኪል እንደገለጹት፥ ድርጅታቸው ከውጭ ይገቡ የነበሩ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ስራን እያከናወነ ይገኛል።

በድርጅቱ የሚመረቱ ምርቶች በጥራትም በአይነትም ሰፊ መሆናቸውን ጠቁመው በሚፈጠር የገበያ ትስስርና የአቅርቦት ሰንሰለት ምርቱን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም