ኮሚሽኑ አለመግባባቶችን ወደ ውይይት በማምጣት በዘላቂነት ለመፍታት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ማህበሩ የበኩሉን ሚና ይወጣል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ አለመግባባቶችን ወደ ውይይት በማምጣት በዘላቂነት ለመፍታት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ማህበሩ የበኩሉን ሚና ይወጣል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ አለመግባባቶችን ወደ ውይይት በማምጣት በዘላቂነት ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የሚታዩ አለመግባባቶችን በምክክርና ውይይት ለመፍታት እንዲቻል ሀገራዊ የሆነ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።
ኮሚሽኑም ከተቋቋመ ጀምሮ በኢትዮጵያ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት አበክሮ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መምሕራን ማሕበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፥ ችግሮችን ለመፍታት ከምክክር እና ውይይት ውጭ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም።
ማሕበሩ በኢትዮጵያ የማያግባቡ ነገሮችን በውይይትና በምክክር ለመፍታት እየተደረገ ባለው የምክክር ሂደት አጋዥ ለመሆን ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር ስምምነት መፈራረሙን ገልፀዋል።
በዋናነትም ሁሉም አካላት ችግሮችንና የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በውይይት፣በምክክርና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ችግሮችን በጠበንጃ አፈሙዝ ለመፍታት ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም መፍትሔ ሊያመጣ አለመቻሉ በተጨባጭ መታየቱንም አመልክተዋል።
በመሆኑም አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ከጠመንጃ አፈሙዝ ይልቅ ውይይትና ምክክርን ማስቀደም እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ሁሉም አካላት ለምክክሩ ስኬት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንደሚጠበቅበትም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
ማህበሩ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ አለመግባባቶችን ወደ ውይይት በማምጣት በዘላቂነት ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ በሁሉም ክልሎች ከወረዳ ጀምሮ ያሉ አባላት ለምክክሩ ስኬታማነት በትብብር እየሰሩ ነው ብለዋል።
ምክክሩ ለኢትዮጵያ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ማሕበሩ ያምናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በመምሕራን መዋቅር መሰረትም አጀንዳ በመለየትም ለኮሚሽኑ ያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።