ቀጥታ፡

ባለሀብቶች በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በመደገፍ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው - አቶ አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ):- ባለሀብቶች በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በመደገፍ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሁለተኛ ዙር  የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።


 

በዕለቱ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንደገለፁት በክልሉ የሚገኙ አልሚ ባለሀብቶች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።

በተለይም ባለሀብቶች በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ ላለው የኮሪደር ልማትና የአስፓልት መንገድ ግንባታ እያደረጉት ያለው የገንዘብ ድጋፍ ልማቱ በተሻለ ፍጥነት እና ጥራት እንዲከናወን አድርጓል ብለዋል።

"የአሶሳ ከተማን የማስዋብ ስራ የነዋሪዎቿ ሀላፊነት ሊሆን ይገባል" ያሉት አቶ አሻድሊ፤ የከተማዋን ዕድገት የሚያረጋግጡ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ይከናወናሉ ብለዋል።

በተለይም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።

ለዚህም ባለሀብቶች በባለቤትነት ስሜት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በከተማዋ የሚገነቡ የመሠረተ ልማቶች ለባለሀብቶች የበለጠ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲያሰፉ የሚያግዝ እንደሆነም አብራርተዋል።

በመጀመሪያ ዙር የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ173 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል መገባቱን ጠቅሰው ከዚህም አብዛኛው ገንዘብ ተሰብስቦ ለአስፓልት እና ኮሪደር ልማት ስራው መዋሉን አንስተዋል።

በዛሬው መድረክም 41 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ቃል ተገብቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም