በክልሉ የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የፋይናንስ አካታችና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የፋይናንስ አካታችና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሰመራ ፤ሚያዝያ 21/2017 (ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የፋይናንሰ አካታችና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
የፋይናንስ አካታችነትና ተደራሽነት ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሰጠ ነው።
የስልጠናውን መድረክ ያስጀመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመር ኑሩ እንዳሉት ስልጠናው ለረጅም ጊዜያት ከፋይናንስ ሥርዓት አገልግሎት ርቆ የቆየውን የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው።
የአርብቶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማሳደግ በሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተደራሽ የፋይናነስ ስርዓት እንዲኖር የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
አካታች ፋይናንስ የዘላቂ ልማት መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ስልጠናውም በማህበረሰቡ ዘንድ የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ የሚያስችል መነቃቃት የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለውን የብሔራዊ ፋይናንስ አካታችንነት ስትራቴጂ አተገባበር እንዲጠናከር መሰል ስልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የፋይናንስ አካታችነት ሴክሬታሪ ዋና አስተባባሪ አቶ አብርሃም ፍቃዱ በበኩላቸው የፋይናንስ አካታችነትን ለማጎልበት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ብለዋል።
የዜጎችን የፋይናንሰ አካታችነትና ተደራሸነትን ለማሳደግ አሁን ላይ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ስልጠናው ለሁለት ቀን የሚቆይ ሲሆን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና ኤፍ.ኤስ.ዲ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በመተባበር ነው።