ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ከ10 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከደረሱ የእሳት እና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ከ10 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኮማንደር መሐመድ አህመድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ 454 አደጋዎች አጋጥመዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 303 የሚሆኑት የእሳት አደጋዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 151 ዱ ደግሞ ድንገተኛ አደጋዎች መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በደረሱት አደጋዎች ከ 556 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ከ10 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከውድመት ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።

በደረሱት አደጋዎች ህይወታቸዉ አደጋ ውስጥ የነበረ 104 ሰዎችን መታደግ መቻሉንም አስታውቀዋል።

ካጋጠሙት አደጋዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው በመኖሪያ ቤቶች ላይ የተመዘገበው ሲሆን በንግድ ቤቶች ላይ ያጋጠሙ አደጋዎች በሁለተኝነት ተቀምጠዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ እና አካባቢዋ የደረሱ አደጋዎችን በፍጥነት መቆጣጠር በመቻሉ ከፍተኛ ሀብት ከውድመት ማዳን መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

ይህም የኮሚሽኑን አደጋዎችን ፈጥኖ በመቆጣጠር የማዳን አቅሙ 97 በመቶ መድረሱን እንደሚያሳይ አመላክተዋል፡፡

ለአደጋ አጋላጭ የሆኑ መሰረተ ልማቶች በአዲስ መልክ መሰራታቸውን ተከትሎ በከተማዋ የአደጋ ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ጥረት ከኮሚሽኑ እየተላለፉ ያሉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ህብረተሰቡ በአግባቡ መተግበሩ ውጤት ማምጣቱን በመጠቆም ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም