ኢትዮጵያ ከብራዚልና ሩሲያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከብራዚልና ሩሲያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለጸች

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከብራዚል እና ሩሲያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች።
የ2025 የመጀመሪያው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ እየተካሄደ ነው።
ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ስብስባ ላይ እየተሳተፈች ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከስብስባው ጎን ለጎን ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ እና ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተወያይተዋል።
ከቪዬራ ጋር በነበራቸው ውይይት ብራዚል በ2025 የብሪክስ ፕሬዝዳንነቷ እያከናወነች ያለውን ስኬታማ ስራ አድንቀው ኢትዮጵያ ለብራዚል የትኩረት አቅጣጫዎች ድጋፍ እንደምታደርግ አመልክተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ሀገራቱ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የግብርና ምርታማነት፣ የዓለም የአስተዳደር ተቋማት ሪፎርም፣ የኢነርጂ ሽግግር እና የደን ልማት ፕሮግራሞች በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳይ ላይም መክረዋል።
ሚኒስትር ማውሮ ብራዚል እ.አ.አ በ2024 የቡድን 20 ፕሬዝዳንት በነበረችበት ወቅት ስትተገብራቸው የነበሩ ኢኒሼቲቮችን በማንሳት ኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፀረ- ረሃብ እና ድህነት ጥምረት ቦርድ አባል በመሆን እያከናወነች ያለውን ስራ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በተያያዘም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ሁሉን አቀፍ ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው ትስስሩን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን የትብብር አማራጮች የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆነች ገልጸዋል።
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከስብሰባው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።