መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የአምራች ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ምርታማነት ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የአምራች ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ምርታማነት ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 21/2017 (ኢዜአ)፡-መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሀብቶች ያነሷቸው የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በማቃለል በኢንዱስትሪ ምርታማነት ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያስችል ተገለጸ፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወቃል።
በማዕከሉም 12 ተቋማት ተቀናጅተው ከ41 በላይ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጥበት ነው።
ይህም ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣የወረፋ ጥበቃን በማቃለል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ስራ መግባቱ በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የሚናገሩት።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን እንደገለጹት፥ የመንግስትን አገልግሎት አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ለማድረግ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወሳኝ ሚና አለው።
ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፥ ቀደም ሲል ባለሃብቶች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ሲያነሷቸው የነበሩ ቅሬታዎችን በመሰረታዊነት እንደሚፈታ አመልክተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጸጋዬ ዘካርያስ በበኩላቸው፥ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚገቡ ባለሃብቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ይህን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግና ዘመናዊነትን የሚያሳልጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ አግልግሎት ነው ብለዋል።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ፅሕፈት ቤት አስተባባሪ አያና ዘውዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በአምራች ኢንዱስትሪው የሚያጋጥሙ ችግሮች በአንድ ቦታ መፍትሄ እንዲያገኝ መደረጉ ጊዜና ወጪን እንደሚቆጥብ ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪው የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ያባክን የነበረውን ጊዜ በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንዲያውለው ያደርጋል ብለዋል።
በመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ስራ ከጀመሩ ተቋማት መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣የብሄራዊ መታወቂያ አገልግሎት፣የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይጠቀሳሉ።
እንዲሁም የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት፣ የኢትዮ ፖስታ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከእነዚህ ወስጥ ናቸው።