ክልሎች በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እያዘጋጁ መሆኑን ገለጹ

አዳማ ፤ሚያዝያ 21/2017 (ኢዜአ)፡-ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እያዘጋጁ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የክልሎች የግብርና ቢሮ የስራ ሃላፊዎች ገለፁ።

ለኢዜአ አስተያየት ከሰጡት መካከል የሐረር ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ፤ ለዘንድሮው አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው  ችግኞች  እየተዘጋጁ ነው።

በተለይ በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራን በስነ ህይወታዊ ዘዴ ለመሸፈን የመሬት ልየታና የችግኝ መትከያ ጉድጓድ እየተቆፈረ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በዚህም 70 በመቶ የፍራፍሬ ችግኝ፣ 30 በመቶ ደግሞ ለደን ልማት አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን  አርሶ አደሩን በማሳተፍ  እየተዘጋጁ   መሆኑን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የባዮ ዳይቨርሲቲ ዳይሬክተር አቶ አሊ ኢብራሂም እንዳሉት በክልሉ በመጪው ክረምት ከ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ከክልሉ የአየር ጸባይ ጋር የሚስማሙ የደን፣ የፍራፍሬና ለእንሰሳት መኖ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞች እንደሚተከሉም ተናግረዋል።


 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብትና የውሃ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ በየነ በላቸው በክልላቸው ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 235 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት አመቺ በመሆኑ በመጪው ክረምት አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬ ችግኝ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መረሀ ግብር በሁሉም ክልሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ለዚህም የችግኝ ዘር በአይነት ከማቅረብ ጀምሮ ችግኞችን የማፍላት ስራ በሁሉም ክልሎች ወጥነት ባለው መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የተከላ መሬት ልየታ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም ለደን አገልግሎት፣ ለምግብነትና የአፈር ለምነትን የሚጨመሩ ችግኞች ዝግጅት ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰው እስካሁን 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም