ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ምእራባዊ አካባቢዎች፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ ምስራቃዊ ክፍል እንዲሁም በሰሜንና ደቡብ ታንዛንያ ከመደበኛው በላይ ዝናብ ይጠበቃል

ሚያዝያ 21/2017 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ምእራባዊ  አካባቢዎች ፣በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ ምስራቃዊ ክፍል እንዲሁም በሰሜንና ደቡብ ታንዛንያ በቀጣዮቹ ቀናት ከመደበኛው በላይ የዝናብ መጠን የሚጠበቅ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት አስታወቀ።

የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ኢክፓክ) የአየር ትንበያ መረጃ እንደሚያመለክተው በምስራቅ አፍሪካ አገራት ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ይጠበቃል። 

በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ምእራባዊ አካባቢዎች ፣በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ ምስራቃዊ ክፍል፣በማእከላዊና ደቡብ ሶማሊያ እንዲሁም በሰሜንና ደቡብ ታንዛንያ ከመደበኛው በላይ ዝናብ ይጠበቃል።

በማእከላዊ እና ምእራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳን በርካታ አካባቢዎች፣ በኡጋንዳ፣ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ምስራቃዊ ኬንያ እና ሶማሊያ መጠነኛ የዝናብ ሰርጭት ይኖራል።

በማእከላዊ ታንዛንያ መጠነኛ ዝናብ ቢኖርም በሌሎቹ የአገሪቷ አካባቢዎች ግን ከፍተኛ የዝናብ መጠን ሊመዘገብ የሚችል መሆኑን ነው ትንበያው የሚያሳየው። 

በመሆኑም ከመደበኛው በላይና ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት በሚኖርባቸው አካባቢዎች በጎርፍ ጉዳት እንዳይደርስ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።

ከቀጣናው አገራት መካከል በደቡብ ሱዳን በርካታ አካባቢዎች በቀጣዮቹ ቀናት ከ32℃ (ዲግሪ ሴንቲግሬድ) በላይ ከፍተኛ የሙቀቱ መጠን ሊመዘገብ ይችላል ተብሏል።

በሱዳን በርካታ አካባቢዎች፤ በኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ኡጋንዳ ከ20-32℃ የሙቀት መጠን የሚኖር ሲሆን በማእከላዊ የኢትዮጵያ ክፍል፤ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ እና የኬንያ ማእከላዊና ምእራብ የአገሪቷ አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ ከ20℃ በታች እንደሚሆን ተገምቷል። 

በምስራቅና ሰሜናዊ የሱዳን ክፍል ደግሞ በቀጣዮቹ ቀናት ከመደበኛው በታች ቅዝቃዜ ሊኖር እንደሚችል የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ICPAC) አመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም